የአስተዳደራዊ ፍርድቤቱ የ2018 በጀት አመት ሪፖርት እና የ2019 በጀት አመት እቅድ ግምገማ አካሄዷል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት ችሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የዲጂታል ፍርድቤት ስርዓት ተዘርግቶ ተከራካሪ ወገኖች ባሉበት ሆነው ክርክራቸውን ማድረግ እና ማስረጃ ማቅረብ እንዲችሉ ተደርጓል።
በተጨማሪም በህግ ባለሙያዎች መካከል ተመሳሳይ የህግ አተረጓጎም እንዲኖር ፍርድቤቱ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ተገማች እንዲሆኑ እና በማስተማሪያ ሰነድነትም የሚያገለግል ጋይድቡክ (Ethiopian Capital Market Guidebook for Judges and Lawyers) ተዘጋጅቶ ይፋ ተደርጓል።
ፍርድቤቱ በበጀት አመቱ በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግብይት ስነ ምህዳር ያለውን ሚናና ኃላፊነት ለመወጣት በአጠቃላይ 18 የስልጠና መድረኮችን በማዘጋጀት 1405 ለሚሆኑ ተሳታፊዎች የመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር ስልጠና ተሰጥቷል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣አማራ፣ሀረሪ፣ሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድቤቶች፣ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድቤት እና ሶማሌ ክልል የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ጋር የካፒታል ገበያ የህግ ማዕቀፍ ስልጠናዎችን በትብብር ለመስጠት የህግና ፍትህ ኢንሰቲትዩት ስርዓተ-ትምህርት አካል ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈርሞ ወደ ስራ ተገብቷል።
በምስራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ አገራት አቻ የካፒታል ገበያ ፍርድቤቶች ጋር ቀጠናዊ እና አህጉራዊ የካፒታል ገበያ ፍርድቤቶች ፎረምን በትብብር ለማቋቋም የሚያስችል የመነሻ ሃሳብ ለሰባት የአፍሪካ ሀገራት (ታንዛንያ፣ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ኡጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሪሺየስ ና ዛምቢያ) ተዘጋጅቶ ተልኳል።
በበጀት አመቱ የታየውን ጥንካሬ በቀጣይ በጀት አመት ማስቀጠል እንደሚገባም ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት ተገልጿል።

