የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድቤት በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት ያዘጋጀው ስልጠና መሰጠት ተጀመረ።
በስልጠናው ከፍትህ ሚኒስቴር ፣ ከከፍተኛ ፍርድቤት ፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ፣ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ከፌደራል ስነምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተወከሉ አመራሮች እና የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
የስልጠናውን መርሀግብር በንግግር የከፈቱት የአስተዳደራዊ ፍርድቤት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ አብነት ዘርፉ በስልጠናው ስለካፒታል ገበያ ምንነት በቂ ግንዛቤ ይገኝበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የካፒታል ገበያ እንደ ሀገር አዲስ በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች አስፈላጊ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
“ለወደፊትም ከተሳታፊ ተቋማቱ ጋር በጋራ የምንሰራ በመሆናችን የትውውቅ ፣ የትስስር እና የቅንጅት አጋጣሚ የሚፈጥር የስልጠና መርሀ ግብር ነው ” ሲሉ አቶ አብነት ተናግረዋል።
የካፒታል ገበያ ምንነትን በተመለከተ ስልጠና የሰጡት ዶ/ር ጠንክር ሰይፉ÷ የገበያውን ምንነትና ምህዳር፣ የገበያው ተሳታፊዎች ሚና፣ የፋይናንስ አካታችነት እና ከሌሎች የገበያ አይነቶች ጋር ያለው ዝምድና ላይ በሰፊው ግንዛቤ ፈጥረዋል።
ዛሬ የተጀመረው የሰነደ ሙዓለ ነዋይ ግብይት እና ቁጥጥርን በተመለከተ የሚሰጠው ስልጠና ከሰዓት በኋላ እና ነገ ቀኑን ሙሉ የሚቀጥል ነው።
