የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድቤት የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የፍርድቤቱን የአገልግሎት አሰጣጥ ስምምነት ሰነድ ግምገማ አካሄደ።
ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከፈጻማቸው ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ የDigital Court System ዝርጋታ፣ የውጪ አቻ ተቋማት ግንኙነት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሰነድ ዝግጅት እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ጎልተው የታዩ አፈጻጸም ናቸው።
ከ Digital Court System አንጻር አስተዳደራዊ ፍርድቤቱ የችሎት ሂደቱን ግልጽነትና ተደራሽነት ለማሳደግ እንዲቻል የችሎት አዳራሹን ጥራት ባላቸው ካሜራዎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የድምጽ ማጉያ እና መቅረጸ ድምጽ በመግጠም እንዲሁም በዳኞችና ተከራካሪ ወገኖች የሚቀረጸው ሙሉ መረጃ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ እንዲቀመጥ ተደርጎ የተደራጀ ሲሆን ሲስተሙ ተገልጋዮች በአካል መገኘት ሳያስፈልጋቸው በዙም መተግበሪያ ባሉበት ሆነው ችሎቱን መከታተል የሚያስችል ስክሪን በማዘጋጀት ወደ ስራ እንዲገባ አድርጓል።
የቨርቹዋል ዙሚንግ የዳኝነት አገልግሎት ሲስተሙና የአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ድረ-ገጽ የተሳሰረ በመሆኑ በአካል ችሎቱን መታደም የማይችሉ ተገልጋዮች የተዘጋጀውን ፎርም በመሙላት የቨርቹዋል ዙሚንግ አገልግሎት ሲጠይቁ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ሊንክ ከደህንነት ስጋት ነፃ በሆነ መንገድ በኢሜይል/ኤስ.ኤም.ኤስ የሚልክ ሲሆን ተገልጋዩም በተላከለት ሊንክ አማካኝነት ችሎቱን መታደም እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ሌላኛው በተቋሙ ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ የታንዛኒያ የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) ለመፈራረም መደረሱና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ማለትም ከኬንያና ናይጄሪያ ጋር እንዲሁ በጋራ ለመስራት የሚያስችል concept note መላኩ ሲሆን ይህም በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ የካፒታል ገበያ ፍርድቤቶች ፎረም ለማካሄድ መሰረት እንዲሆን የታሰበ ነው።
አስተዳደራዊ ፍርድቤቱ ከ 7 ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ 491 ተሳታፊዎች በተለያዩ አምስት ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም የካፒታል ገበያ የህግ ማዕቀፍ፣ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ተግባራት፣ ለህዝብ የሚሸጡ ሰነዶችን ይፋ የማድረግ ሂደት እና ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች፣ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች እና የገበያው ተሳታፊዎች፣ በካፒታል ገበያ የተከለከሉ ተግባራት ምንነት እና የሚያስከትሉት ተጠያቂነት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች አካሄዷል።
በተጨማሪም በአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ላይ ተመስርተው አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዮችን እርካታና ተቋማዊ አመኔታ ለማሳደግ ያለመ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቷል።
ረቂቅ ሰነዱ የአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱን አገልግሎቶች አይነትና ብዛት እንዲሁም ለተገልጋይ ከሚሰጡ አገልግሎቶቹ ባህሪ አንፃር ስታንዳርድ በማውጣት የአገልግሎት አሰጣጥ ስምምነት መሆኑም ተመላክቷል።
