የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ከሲዳማ ክልል የፍትህ ተቋማት ለተወጣጡ ዳኞች፣ አቃቢያነ ህግ እና ከፍተኛ አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው።
አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ በሀዋሳ ከተማ ከሲዲማ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፍትህ ቢሮ፣ ከስነ ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ፣ከፖሊስ ኮሚሽን እና ከርዕሰ መስተዳደሩ ጽ/ቤት ለተወጣጡ ዳኞች፣ አቃቢያነ ህግ እና ከፍተኛ አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ አብነት ዘርፉ: የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ስለ ካፒታል ገበያ ምንነት፣ የካፒታል ገበያ የህግ ማዕቀፎች እና የገበያው ተዋንያን ሃላፊነት እንዲሁም በገበያው ውስጥ የተከለከሉ ተግባራትን እና የሚያስከትሉትን ተጠያቂነት መረዳት ለግብይቱ ስርአቱ ስኬት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሲዳማ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደምሴ ዱለቻ የካፒታል ገበያ በሀገራችን መጀመሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን በማሳለጥ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።
አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ስለ ካፒታል ገበያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ማዘጋጀቱ በክልሉ ለሚገኙ የፍትህ ተቋማት ዳኞች፣ አቃቢያነ ህግ እና ከፍተኛ አመራሮች በዘርፉ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ሲሉ አቶ ደምሴ ተናግረዋል።
በተጨማሪም አስተዳዳራዊ ፍርድ ቤቱ ከሲዳማ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በጋራ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ስኬት ተቋማችን ዝግጁ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
