የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድቤት ከሶማሌ ክልል የዳኝነት፣ የፍትህና ፋይናንስ ሴክተር ተቋማት ለተወጣጡ ዳኞች፣ አቃቢያነ ህግ እና ከፍተኛ አመራሮች ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
ፍርድ ቤቱ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ወይም የባለስልጣኑን ስልጣን የሚያስፈጽም ሰው በካፒታል ገበያ አዋጅ፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ህጎች መሰረት የሰጡትን ውሳኔዎች በይግባኝ የመመርመር ስልጣን አለው።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔዎቹን ሊያጽና፣ ሊሻር ወይም ሌላ ተገቢ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል።
የፍርድ ቤቱ ስልጣን በባለስልጣኑና በሰነደ ሙዓለ-ንዋይ ገበያው ወይም ራሱን በራሱ የሚቆጣጠር ድርጅት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን፣ በባለስልጣኑና በግብይት ተሳታፊዎች መካከል፣ በተሳታፊዎች እርስ በርሳቸው እና ከደንበኞቻቸው/ኢንቨስተሮች ጋር የሚነሱ ጉዳዮችን ያካትታል።
እንዲሁም የምዝገባ ውድቀት፣ የፈቃድ መታገድ ወይም መሰረዝ፣ ከገበያ መዝገብ ማስወገድ እና በካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ወይም በገበያው ድርጊት ምክንያት የገንዘብ ጉዳት የደረሰባቸው ኢንቨስተሮች የካሳ ፈንድ ጥያቄዎችን እንደሚያስተናግድ ተሳተፊዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል።
