የተከበሩ አቶ አብነት ዘርፉ አብርሃም
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ
የተከበሩ አብነት ዘርፉ አብርሃም የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት የመጀመሪያው መስራች ሰብሳቢ ዳኛ ሲሆኑ የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ፍርድ ቤቱን ውስጣዊ አደረጃጀት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ስትራቴጂያዊ አመራር በመስጠት እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የድምፅ እና ምስል ቀረጻ የቪዲዮ ኮንፈረንስን ያካተተ ዘመናዊ የችሎት ስርዓት እንዲኖረው በማድረግ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ቀልጣፋ፣ ግልጽና ታማኝ የዳኝነት አካል ለመመሥረት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
በትምህርት ደረጃ በዓለም አቀፍ ሕግ (International Law) የሁለተኛ ዲግሪ (LL.M) ፣ በፆታና ልማት ጥናት (Gender and Development Studies) የማስተርስ ዲግሪ (MA) እንዲሁም በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ (LL.B) አላቸው። በተጨማሪም በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኘው Chartered Institute of Securities and Investment (CISI) አለምአቀፍ ሰርተፍኬት አላቸው፡፡
ስራ ልምዳቸውን በተመለከተ ተለያዩ የመንግስትና የሕዝብ ተቋማት ውስጥ ማለትም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሕግ አስተያየቶችና ዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ጠቅላላ ዳይሬክተር፣ በኢትዮጵያ የምርት ገበያ ባለስልጣን የአስተዳደር ፍርድ ቤት ዳኛ፣ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፍትሕ ቢሮ ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ እንዲሁም የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም ቡድን መሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡
የተከበሩ አቶ አብነት ዘርፉ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ተቋሙን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማደራጀት፣ ባለጉዳዮች በቀጠሮ ቀን በአካል መገኘት ሳይኖርባቸው በቪዲዮ ኮንፈረንስ ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲከታተሉ የሚያስችል ተደራሽ ችሎት ስርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ በታታሪነት ሰርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም የአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ወጥ የሆነ የካፒታል ገበያ የህግ አተረጓጎም እና ተፈፃሚነት እንዲኖራቸው የሚስችል የአሰራር መመሪያ እንዲዘጋጅ አድርገዋል፡፡